የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን ከ30 በመቶ ወደ 17 በመቶ ዝቅ እንዲል አግዟል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የዋጋ ንረት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 17 በመቶ ዝቅ እንዲል አግዟል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ በጥብቅ ዲሲፒሊን እየተመራ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤት እያስገኘ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ለአብነትም የብር ምንዛሪ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን በመደረጉ ወርቅ አምራቶች ምርታቸውን በማዕከላዊ ገበያ ለብሔራዊ ባንክ እንዲሸጡ አነሳስቷቸዋል ብለዋል፡፡
ማሻሻያው ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ድርጅቶችን እያጠናከራቸው እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት፣ ለስራ እድል ፈጠራ እና ለሸቀጦት ዋጋ መረጋጋትም ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ተግበራዊ የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ መንግስት ከግምጃ ቤት የሚበደረውን የገንዘብ መጠን እንዲገደብ እና ባንኮች የሚሰጡት የብድር መጠን በ18 በመቶ ብቻ እንዲያድግ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ከኢኮኖሚ እድገቱ ጋር የተመጣጠነ የገንዘብ አቅርቦት እና ፍሰት በገበያ ውስጥ እንዲኖር በማስቻል የዋጋ መረጋጋት እንዲኖር እና አምራቾች እንዲበረታቱ በማድረግ ውጤታማ ሊሆን መቻሉን አብራርተዋል።
የገንዘብ ፖሊሲው መተግበር የዋጋ ንረት ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 17 በመቶ ዝቅ እንዲል እገዛ ማድረጉንም አንስተው፤ ማሻሻያው የባንኮች ቁጠባ እንዲያድግ እና ለኢኮኖሚ የሚያቀርቡት ብድር እየተጠናከር እንዲሄድ ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
የዋጋ ንረቱ ከነበረበት ዝቅ ብሏል ማለት የሸቀጦች ዋጋ አልጨመረም ማለት አይደለም፤ የኑሮ ውድነትን ቀንሷል ማለት እንዳልሆነም አብራርተዋል፡፡
በአንጻሩ የዋጋ ንረቱ ከነበረበት ዝቅ ብሏል ማለት የሸቀጦች ዋጋ በየአመቱ ያድግ ከነበረበት 30 በመቶ ወደ 17 በመቶ ዝቅ ብሎ እንዲያድግ ረድቷል ማለት ነው ብለዋል፡፡
የሸቀጦችን የዋጋ እድገት መቼም ቢሆን ማቆም አይይቻልም፤ ይህ ከሆነ እድገት ይቆማል ወይም ይገታል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይልቁንስ እድገቱ ጤናማ እንዲሆን ማድረግ ነው የሚቻለው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ለዚህም የዋጋ ጭማሪው ከሁለት አሃዝ በታች እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለመከላከልም በገበያ ውሥጥ በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ለስትራቴጂክ እና መሰረታዊ ሸቀጦች በተለይም ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለዘይት፣ ለመድሃኒትና ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ድጎማና ለሌሎች ከ400 ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ እያደረ ይገኛል ብለዋል፡፡
በመስኖ ልማት ብቻ እስካሁን 3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በዘር መሸፈኑን ጠቁመው÷ ይህም ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የነደፈችውን ትልም ለማሳካት መሰረት እንደሚጥል ይታመናል ብለዋል፡፡
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት እና የግብርና ስራዎች የበጋ ወቅት ርብርብ ማዕከል ሆነው መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
በሚቀጠሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ከተረጂነት እና ጠባቂነት የሚያላቅቁ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ለመጪው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ እና ሌሎች ኮንፈረንሶች አስፈላጊው ዘርፈ ብዙ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ