Fana: At a Speed of Life!

በትምሕርቱ ዘርፍ ለኢትዮጵያ የማደርገው ድጋፍ ይቀጥላል- ጀርመን

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጀርመን በኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት የወደሙ ትምሕርት ቤቶችን መገንባትን ጨምሮ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ድጋፏ እንደሚቀጥል አረጋገጠች፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ከሆኑት ጄንስ ሃንፊልድ ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅትም ለዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ በማድረግ ተወዳዳሪና ብቁ ትውልድ ለመፍጠር እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ሥራዎችን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትምህርት ዘርፉ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ጨምሮ ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮችንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ፣ ነጻ ሃሳብ የሚራመድባቸው፣ ትክክለኛ የማስተማሪያና የምርምር ተቋማት እንዲሆኑ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎችን እንዲደግፉ ጠይቀዋል።

አምባሳደሩ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጀርመን ለረጅም ጊዜ የቆየ መልካም ግንኙነት ዳላቸው አውስተው፤ ሀገራቸው ይህን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጀርመን ትምህርት ቤት ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎች÷ የነጻ የትምህርት ዕድል የሚያገኙበትን፣ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ በመገንባትና በትምህርት ዘርፉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን በመደግፍ ረገድ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.