ኢትዮጵያና ኪርጊስታን ኢኮኖሚያዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከኪርጊስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አሲዬን ኢሳዬቭ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በኢትዮጵያና ኪርጊስታን መካከል ያለውን ኢኮኖሚናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አቶ አሕመድ ሺዴ÷ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ በሚገኙ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሰብ ሰሃራ ሀገራት በኢኮኖሚ እድገት 3ኛ መሆኗን ጠቁመው÷ ለዚህም በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተደረጉ ማሻሻዎች አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በአረንጓዴ አሻራ ያላትን ተሞክሮ ለኪርጊስታን ለማጋራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
አሲዬን ኢሳዬቭ በበኩላቸው÷ በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብርና ተሞክሮ የመጋራት ልምድ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኪርጊስታን በረራ በመጀመር የሀገራቱን ትስስር ይበልጥ እንዲያጠናከር ሃሳብ መቅረቡንም በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡