ከ24 ሺህ በላይ ዜጎችን ከጎዳና ተነስተዋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ከ24 ሺህ በላይ ዜጎችን ከጎዳና ማንሳት መቻሉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንደገለፁት÷ ከጎዳና ከተነሱ ወጎኖች ውስጥ 908 ህፃናት ይገኙበታል።
ዜጎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት የተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸው፤ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ወደ መጡበት አካባቢና ቤተሰቦች ተመልሰው እንዲቋቋሙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ከጎዳና ላይ የተነሱ፣ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት የተለያዩ አገልግሎቶችን ያገኙ እና ወደ ቤተሰቦቻቸውና ማሕበረሰቡ የተቀላቀሉ፣ የተዋሃዱና የተቋቋሙ ወገኖችን ቁጥር 86 ሺህ 500 መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከጎዳና የሚነሱ ዜጎች ቁጥር እና ያሉት የጊዜያዊ መጠለያ ማገገሚያ የሚመጣጠን አለመሆን ተግዳሮት እንደሆነ ጠቁመዋል።
የበጀት ውሱንነት መኖሩ እንዲሁም በተሳሳተ አመለካከትና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ከተሞች የሚደረግ ፍልሰት አሁንም ያለመቋረጡ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ፈተና መሆኑን ተናግረዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና ዜጎች የተሻለ የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎት እንዲያገኙ ተጨማሪ ሀብት ከማሰባሰብ ጎን ለጎን የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቀናቄ ማድረግ ያስፈልጋል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡