Fana: At a Speed of Life!

የፋሲል ግንብ ነባር ይዞታውን ይዞ ታድሶ ወደነበረው ግርማ ተመልሷል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጥንታዊው የፋሲል ግንብ ነባር ይዞታውን ይዞ ታድሶ ጥንት ወደነበረው ግርማ ሞገስ ተመልሷል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ጎንደር እምነት፣ መንግሥት እና ኅብረ ብሔራዊነት ተሸምነው የሠሯት ከተማ ናት ብለዋል።

ነገሥታቱ ሥርዓተ መንግሥትና አብያተ መንግሥት አቁመዋል፤ የእምነት መሪዎች አብያተ ክርስቲያናትና መስጊዶችን ተክለዋል፤ እነዚህን ሁለቱን ፍለጋ ከመላ ኢትዮጵያና ከውጭ የመጡ ሰዎች ደግሞ ጎንደርን ኅብረ ብሔራዊት ከተማ አድርገዋታል ሲሉ ገልጸዋል።

የጎንደር ጥምቀት በዓል ጎንደር የመንግሥት፣ የቤተ እምነትና የኅብረ ብሔራዊነት ማዕከል በመሆኗ ካቆየቻቸው ዕሴቶቿ አንዱ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

ከጣት ጣት ይበልጣል እንዲሉ አንዳንድ ነገር በአንዳንድ ቦታ ይደምቃል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በጎንደር የሚያከብር ሰው ለጎንደር ትንሣኤ ምስክር ነው ብለዋል።

ጥንታዊው የፋሲል ግንብ ነባር ይዞታውን ይዞ ታድሷል፤ ጥንት ወደነበረው ግርማ ሞገስ ተመልሷል ሲሉም አክለዋል፡፡

ከተማው እንደ ሙሽራ እያበበ ነው፤ እነ ዐፄ ፋሲል፣ ዐፄ ቴዎድሮስ ቢመጡ በአድናቆት ከተማቸውን መልሰው መጎብኘታቸው አይቀሬ ነው ሲሉም የከተማዋን ውበት አድንቀዋል፡፡

የጎንደር ማንሠራራት የኢትዮጵያ ማንሠራራት አንዱ ማሳያ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.