ከ372 ሚሊየን ብር በላይ የተመዘበረ የመንግስትና የህዝብ ሀብት መመለሱ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ372 ሚሊየን ብር በላይ የተመዘበረ የመንግስት እና የህዝብ ሀብት ማስመለሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽነር ሶፎንያስ ደስታ÷በግማሽ ዓመቱ 36 የሙስና ጥቆማዎች ለተቋሙ መድረሳቸውን ገልፀው በዚህም 6 ሚሊየን 908 ሺህ 789 ብር ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ስምንት የመንግስት ቤቶች፣ አንድ ሀሰተኛ የይዞታ ማረጋገጫ እና ሌሎች የመንግስትና የህዝብ ሀብት በቅድመ መከላከል ስራ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በ6 ወራት በተከናወነ የብልሹ አሰራር እና የፀረ ሙስና ትግል ከ17 ሺህ ካሬ በላይ የከተማ መሬት፣ 30 ሄክታር የገጠር እርሻ ይዞታ እና ሌሎች የመንግስትና የህዝብ ሀብት ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለሱ ማድረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ 372 ሚሊየን 945 ሺህ 11 ብር የተመዘበረ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ማስለስ ተችሏል ሲሉ ኮሚሽነር ሶፎንያስ መጥቀሳቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።
በተያያዘ በግማሽ ዓመቱ የ10 ሺህ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ሀብት ለመመዝገብ ታቅዶ የ11 ሺህ 3 አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ሀብት መመዝገብ መቻሉንም ተናግረዋል።