የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ ከሃማስ ጋር የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነትን አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ ከትናንት በስቲያ በሃማስ እና እስራኤል መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በዛሬው ዕለት አጽድቋል፡፡
ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የወጣው መግለጫ እንደሚያመላክተው÷ካቢኔው ሁሉንም የፖለቲካ፣ የፀጥታ እና ሰብዓዊ ጉዳዮችን ከመረመረ በኋላ የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመደገፍ አጽድቋል።
ካቢኔው አሁን የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል ለማሳካት አስባ የነበረውን ግብ እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
የጸጥታ ካቢኔው በመጨረሻም መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲያጸድቅ ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን አልጀዚራ ዘግቧል።
በጸጥታ ካቢኔው ድጋፍ ያገኘው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ወደ ዋናው ካቢኔ እንደሚመራም ተመላክቷል፡፡
በሶስት ምዕራፍ የሚተገበረው ይህ የእስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ከመጪው እሑድ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ስምምነቱ በዋናው የቤኒያሚን ኔታኒያሁ መንግስት ካቢኔ የሚጸድቅ ከሆነ ለ15 ወራት የቆየውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በዘላቂነት ሊያስቆም እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡
በተመሳሳይ ሃማስ ከእስራኤል ጋር የደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳጸደቀ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡