ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ የልማት ጉዞ በርካታ ተግባራትን በቁርጠኝነት በማከናወን ላይ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
“ኢትዮጵያ አረንጓዴ ጉዞ 2030” በሚል መሪ ሃሳብ አመታዊ የልማት ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በኮንፈረንሱ የተገኙት ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በያዘችው የልማት እቅድ የአየር ንብረትንና አረንጓዴ ልማትን አጣምራ እየሰራች እንደምትገኝ አንስተዋል።
ዓለምን እያሰጋ የሚገኘውና በፍጥነት እየተለወጠ የመጣው የአየር ንብረት ችግRን ለመቅረፍ ፣ በትብብር በመስራት አፋጣኝና ወሳኝ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል ውጤታማ ስራ እየሰሩ የሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትን ማገዝና መደገፍ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ የልማት ጉዞ በርካታ ተግባራትን በቁርጠኝነት በማከናወን ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም 40 ቢሊየን ችግኝ መትከሏን በማድነቅ የፓሪስ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ያሳየችውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የምታከናውናቸው በርካታ ተግባራት የተፈጥሮ ሃብቶቿን ለመጠበቅ የወሰደችውን ቁርጠኝነት ያሳያል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ለምትሰራው ስራ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት በማስታወቅ በዚህ ረገድ የግል ሴክተሩ አጋርነት በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡