Fana: At a Speed of Life!

15ኛው ዓለም ዓቀፍ የምልክት ቋንቋ ጥናትና ምርምር ጉባኤ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተካሄደው 15ኛው ዓለም ዓቀፍ የምልክት ቋንቋ ጥናትና ምርምር ጉባኤ ተጠናቀቀ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፤ በጉባኤው የመስማት ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን መብቶች እና እድሎች ለማሳደግ በትብብር፣ በፈጠራ እና በጋራ መስራት ጥቅም እንዳለው ታይቷል።

የምልክት ቋንቋዎች በዓለም ዙሪያ ተጠብቀው እንዲቆዩ፣ እንዲከበሩ፣ እንዲተዋወቁ እና በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲዋሃዱ ማድረግ የጋራ ኃላፊነት እንዳለብን አጽንኦት የተሰጠበት ነው ብለዋል።

ለተደራሽነት ቅድሚያ የሚሰጡ ፖሊሲዎችን፣ መስማት የተሳናቸውን ማህበረሰብ ክፍሎች የሚደግፉ እቅዶች እና ለውጥ የሚያመጡ ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተ የሀሳብ ልውውጥ የተደረገበት ጉባኤ እንደነበር አንስተዋል።

ጉባኤው ሰብአዊ ክብርንና እኩልነትን ለማስከበር ራሳችንን የምንፈትሽበትና ቃል የምንገባበት ነው ማለታቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሂውማኒቲ፣ የቋንቋ፣ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ዲን አማኑኤል አለማየው (ዶ/ር) በበኩላቸው ጉባዔው ዩኒቨርስቲው በምልክት ቋንቋ ዘርፍ እየሠራ ያለውን ስራ እንደሚያጠናክርለት ተናግረዋል።

በጉባኤው በተለያዩ ሀገራት በምልክት ቋንቋ ላይ የተሰሩ ጥናቶች ቀርበው የተገኙ ልምዶች እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ የልምድ ልውውጥ ተደርጓል።

16ኛውን ዓለም ዓቀፍ የምልክት ቋንቋ ጥናትና ምርምር ጉባኤ ስዊድን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.