ማርታን በገሀዱ ዓለም አየኋት!
አብያተ ክርስቲያናቱ ታቦታቱ ከመንበራቸው መውጣታቸውን በደወል አውጀዋል … ሕዝበ ክርስቲያኑም ጥሪውን ተቀብሎ እንደመክሊቱ እንደስጦታው ያጅብ ይዟል።
በአረንጓዴ በቢጫ ቀይ በተንቆጠቆጠው ጎዳና በልብሰ ተክህኖ የደመቁ ካህናትና የግማደ መስቀሉን አምሳል ያነገቡ ዲያቆናት ቅዱስ ቃሉን በዜማ ያወርዱታል… ጽናጽሉ ይንሿሿል፤ የኢየሱስ ክርስቶስ የባህሪ አምላክነት ምሳሌ የሆነው ከበሮ ከሩቅ ይሰማል …. ጥንግ ድርብ ያገለደሙ ሊቃውንት በመስመር ይተማሉ….. ሰንበት ተማሪዎች መጽአ ቃል እምደመና ዘይብልን….ሃሌ ሃሌ ሃሌ ሉያን…. ኢየሱስ ሖረ ሀገረ እሴይን….ሃዲጎ ተሳዓ ወተስዓተ ነገደ ነገደን… ዮሐንስን ያጠመቀን በፍጹም መንፈሳዊ ስሜት ይዘምሩታል… እናቶች ላሎ መንገዱን አለስልሰው ከርሞ ይመጣል የዳነ ሰው ሲሉ የጎረምሶቸ ሆታ ምድር ያንቀጠቅጥ ይዟል.. ብቻ እምነትና ሐይማኖት መዋደድና ክብር ፍቅር ጥበብና ተስፋ በመልከ-ብዙነት ውስጥ ያለ አንድነት መንፈሳዊነት በተሰኘ ቦይ ደርዝ ይዘው ቀለም ፈጥረው ሲፈሱ ምድር ላይ ስለመሆንህ መጠየቁ አይቀሬ ነው!
ወዲህ ደግሞ ማለዳውን እግሯን ስትዘረጋ በስስትና ወርቃማ ቀለሟ የተናፈቀችው ጀንበር አናት ካልበሳሁ ትል ይዛለች … ጀንበር መጽሐፍ የእስራኤል የምርኮ ዘመን ትንቢት ታሪክ ተጋሪው አቤሜሊክ የገጠመውን የፀሐዩ ክረት አፈዘዘው ዓይነት ሃሩር ብትለቅም መንፈሳዊነትን የተቀዳጀው ባለ እምነቱ ምዕመን ግን በደስታ፣ በልልታና በሆታ ታቦታቱን ያጅባል፡፡
በዚህ ሁሉ ድባብ ውስጥ በከፍታ ሳዘግም ነበር በዮሐንስ ወንጌል የሰፈረችውንና በደግነት የማውቃትን ዓይነት ሴት ያየኋት… ማርታ!
አዎ ስድስት ኪሎ አንደኛው ጠርዝ ድንኳን ደኩና እንደነገሩ ለብሳ ግን የደግነት ልክ የሆነ ፈግታን አስቀድማ ፍቅርን በፈሳሽ መልክ የምታድለዋን ማርታን አገኘኋት።
የጋሽ ወንድይፍራው ልጅ ማርታ ታቦታቱን በፍጹም ፍቅርና ትጋታ አጅበው ቁልቁለቱን ወርደው ዳገቱን ለወጡ ታዳሚዎች ከከተራው የሕይዎት ውኃ ባሻገር የሐሩሩ ጥም ቆራጭ ናት።
ማርታ እንደማለዳ ጀንበር በሚሞቅ ፈገግታዋ ደግሞ እንደ እናት ሆድ ስፍስፍ በሚል ፍቅሯ ምእምኑን በሯ ካለ የቧንቧ ውኃ ጠልፋ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም በሚሰጡ የፕላስቲክ ኩባያዎች ፍቅር በውኃ መልክ ታድላለች፤ ጥም ትቆርጣለች።
ዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደአነበብኳትና እንግዳ መቀበል እንደሚያጓጓትና እንደምታስተናግደው ማርታ የስድስት ኪሎዋ ማርታ በግብር ስተመስላት አየሁ።
ይህ የማርታ ወንድይፍራው በጎ ምግባር ከወዳጆቿና ጓደኞቿ ጋር በመሆን ላለፉት ሰባት ዓመታት ያለማቋረጥ የቀጠለ መሆኑን ባወቅሁ ጊዜ ጽናቷና እምነቷ አሁንም የመጽሐፍ ቅዱሷን ማርታ ድጋሜ አስታውሶኛል።
የአልአዛር እህት ማርታ ወንድሟ ሲታመም አምላኳ እንደሚፈውሰው ከዛም ሲያልፍ ከሞት እንደሚያስነሳው የነበራትን አይነት እምነትና ጽናት ዓይነት!
እናም ይቺ ባይኔ የማያት የስድስት ኪሎዋ ማርታ ወደ ባሕረ-ጥምቀቱ ወደ ጃንሜዳ የሚተሙትን የቻለችውን ሁሉ ውኃ ስታጠጣ፣ ንፍሮ ስታዘግን፣ ዳቦ ስታስቆርስ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡
ይሁ ሁሉ ደግነት ደግሞ ከራሷና ከወዳጆቿ ኪስና መቀነት ተቆጥቦ በኩራትና በክብር ከሚመዘዝ ፍራንክ የሚከወን መሆኑ ነው።
የማርታ በጎነት ለጥምቀት ታዳሚዎች ብቻ ሳይሆን በመንገዱ ለሚያልፉ ለሚያገድሙም የሚቸር መሆኑ ደግም የጥምቀቱን ዋና ዓውድና አስተምህሮ ትህትናን መልክ የሚሰጠው ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
በዮናስ ጌትነት