ቻይና የደቡብ ለደቡብ ትብብር የምርምር ማዕከል እንደምትገነባ ገለፀች
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና የታዳጊ ሀገራት የልማት ትብብር የሆነውን የደቡብ ለደቡብ ትብብር (SSC) የምርምር ማዕከል እንደምትገነባ አስታውቃለች፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በቻይና የልማት ጥናትና ምርምር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሉ ሁዋዎ ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያተዋል፡፡
በውይይታቸው ሚስተር ሉ ሁዋዎ÷ ቻይና ከአፍሪካ እና ደቡብ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመው ሶስተኛውን የቻይና አፍሪካ ትብብር ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን አንስተዋል፡፡
የቻይና መንግስት የደቡብ ሀገራትን ከሰሜን ሀገራት እና ባለድርሻ አካላትን ማስተሳሰር የሚችል የደቡብ ለደቡብ ትብብር የጥናት ማዕከል ለመገንባት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ ሲቋቋም የደቡብ ታዳጊ ሀገራት የፖሊሲ እና የልምድ ልውውጥ እንዲያካሂዱ በማድረግ ለዘላቂ እድገታቸው ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበዋል፡፡
አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፥ የደቡብ ለደቡብ ትብብር የምርምር ማከል መገንባቱ ለአፍሪካ እና ለእስያ ታዳጊ ሀገራት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ቻይና ለአፍሪካ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸው፥ የቻይና እድገት የአፍሪካም እድገት ነው ብለዋል፡፡
የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ እና ሌሎች ሴክተሮች እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡