አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለዩጋንዳ እና ኬንያ ፕሬዚዳንቶች ከጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተላከ መልዕክት አደረሱ
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተላከ መልዕክት ለዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሰቬኒ እና ለኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አድርሰዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁለቱ መሪዎች መልካም ጉርብትና እና ቀጣናዊ ትብበር እንዲጠናከር ለተጫወቱት በጎ ሚና እንዲሁም ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ላሳዩት ቀናነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቶቹም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት እና በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር እንዲሁም በራሷ አቅም በሶማሊያና በሌሎችም ሀገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያበረከተችውን አይተኬ ሚና በማውሳት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየተጫወቱት ያለውን ጉልህ ሚና አድንቀዋል።
በቀጣይም በሶማሊያ ሰላምና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ የሚኖራትን ወሳኝ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን ድጋፍና እምነት ገልፀዋል።
ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጎልበትና በኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና እንዲሰፍን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እያደረጉት ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።
የሀገሪቱ የፀጥታና ደህንነት ተቋማትም ለኢትዮጵያ አቻዎቻቸው አስፈላጊውን ትብብር እንዲለግሱ መመሪያ መስጠታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ አስታውቋል።