በወንዶ ወረዳ የተቀሰቀሰውን ሰደድ እሳት መቆጣጠር ተቻለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በወንዶ ወረዳ ጎቱ ኦሎማ ቀበሌ በተለምዶ አባሮ ተራራ ደን በመባል በሚታወቀዉ ስፍራ ትናንት ቀን 10:00 ላይ የተቀሰቀሰውን ሰደድ እሳት መቆጣጠር መቻሉን የወረዳዉ አስተዳደር ገለጸ።
እሳቱ በከፍተኛ ሁኔታ በንፋስ ሀይል ወደ ጥቅጥቅ ደን እየተንቀሳቀሰ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።
አሁን በቁጥቋጦዎች ላይ ከሚታይ ጭስ በስተቀር እሳቱ መቆሙን ወረዳዉ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ወረዳው አረጋግጧል።
እሳቱ 40 ሄክታር ያህል ቦታ ማዳረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ እሳቱን ለመቆጣጠር በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ፣ የአካባቢዉ ማህበረሰብ እና የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ አድርገዋል።
የኮሌጁ ዲን ተሻለ ወ/አማኑኤል (ዶ/ር)፤ እሳት የማጥፋቱ ስራ ላይ የኮሌጁ ማህበረሰብ መሳተፉን ጠቅሰው፤ ከሰደድ እሳቱ ቀድሞ ዛፍ በመቁረጥና ሳር በማንሳት እንዳይዛመት ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
መጀመሪያ የነበረዉ ነፋስ አቅጣጫዉን መቀየር ሰደድ እሳቱ እንዲቀዛቀዝ ማገዙን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ክስተቶች ማጋጠሙን አስታውሰው፤ ማህበረሰቡ በእያንዳንዱ እሳት አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከወረዳዉና አጎራባች ቀበሌ አስተዳደሮች ጋር በመተባበርም የጥንቃቄ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሥራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ፋና ዲጂታል ትናነት ከቀኑ 10:00 ላይ የሰደድ እሳት አደጋው መከሰቱን፣ አደጋውን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን መዘገቡ ይታወቃል።
በጌታቸዉ ሙለታ