Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ አስደናቂ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን አይተናል- የውጭ አገር ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አስደናቂ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን አይተናል ሲሉ በጂንካ ከተማ የጥምቀት በዓልን የታደሙ የውጭ አገር ጎብኚዎች ተናገሩ።

የጥምቀት በዓል በጂንካ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

በዓሉን የታደሙት የውጭ አገር ጎብኚዎች ኢትዮጵያ አስደናቂ ባህል ያላት ሀገር መሆኗን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ከሀገረ ስዊድን የመጡት ሲልቪያ ቾሌት፤በኢትዮጵያ በነበራቸው የአንድ ሳምንት ቆይታ ድንቅ ባህሎችን እና አስገራሚ ቅርሶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በአሪ ዞን እና በደቡብ ኦሞ ዞን በነበራቸው ቆይታ አስደማሚ ባህሎችን መመልከታቸውን ገልፀው÷በዚህም መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ዛሬ እየተከበረ ባለው የጥምቀት በዓል ላይም የምዕመኑ አለባበስ፣ ዝማሬና የካህናት ወረብን የመሰሉ ድንቅ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ክዋኔዎችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ከስዊዘርላንድ የመጡት አድሃኔ ኤይሻል በበኩላቸው÷”ኢትዮጵያ ከጠበኩት በላይ አስደማሚ አገር ሆና አግኝቻታለሁ” ብለዋል።

በአገሪቱ ከሚከበሩ ደማቅ በዓላት አንዱ በሆነው የጥምቀት በዓልን በመታደማቸው መደሰታቸውን በመግለጽ ባዕሉ፣ ሐይማኖታዊ ስርዓቱ እና የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት እንደማረካቸው መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.