ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና ከ908 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በያዝነው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት 908 ነጥብ 47 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ገቢው የተገኘው ለውጭ ገበያ ከተላከ 204 ሺህ 206 ነጥብ 63 ቶን የቡና ምርት መሆኑን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ ሻፊ ኡመር ዛሬ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡
አፈጻጸሙም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ86 ሺህ 251 ነጥብ 17 ቶን ወይም 73 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
እንዲሁም በገቢ ደረጃ የ337 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወይም 59 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው በመግለጫቸው ያነሱት፡፡
በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ 133 ሺህ 63 ነጥብ 49 ቶን የቡና ምርት በመላክ 714 ነጥብ 99 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ንዑስ ዘርፍ ለማግኘት የታቀደውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ገቢ ለማሳካት ዝርዝር ዓመታዊ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱንም አመላክተዋል፡፡
በዕቅዱ ላይም የግብይት ተዋንያኑን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት በመሥራት የኤክስፖርት መጠን እንዲያድግ እንዲሁም ምርቶቻቸውን በጥራት ወደ ውጭ መላክ እንዲችሉ መስማማት ላይ በመድረስ የበጀት ዓመቱ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው