ዓለም ትሪሊየነሮችን በማፍራት መንገድ ላይ …
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም በ10 ዓመት ውስጥ ትሪሊየነሮችን ልታፈራ መንገድ ላይ መሆኗን ኦክስፋም በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
የዓለም ቱጃሮች የሃብታቸው መጠን በፍጥነት እያደገ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የቴስላ እና ስፔስኤክስ ባለቤት ኤለን መስክ በአሁኑ ወቅት 430 ቢሊየን ዶላር ሃብት በማፍራት የዓለም ቁጥር አንድ ባለሃብት ነው፡፡
በዚህም፥ መስክ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ትሪሊየነር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል እንደሲኤንኤን ዘገባ፡፡
የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ፣ የኦራክል ላሪ ኢሊሶን፣ የሜታው ማርክ ዙከርበርግ እና የኤልቪኤምኤች ዋና ሥራ አስፈጻሚ በርናርድ አርናልት እና ቤተሰቦች የትሪሊየነሮችን ጎራ ይቀላቀላሉ ተብሏል።
ፎርብስ ያጠናቀረውን መረጃ መነሻ ያደረገው በዓለም ያለውን ኢ-እኩልነት ለመዋጋት የተቋቋመው ኦክስፋም ሪፖርት በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከሚካሄደው ዓመታዊው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መክፈቻ ጋር እንዲገጣጠም መደረጉ ተገልጿል፡፡
በዚህም አንዳንድ ባለጸጎች እና የዓለም መሪዎች ተገኝተዋል ነው የተባለው፡፡
በፈረንጆቹ 2024 ለዓለማችን በጣም ሀብታም ግለሰቦች እና ቤተሰቦች በጣም ትርፋማ ዓመት እንደነበር የገለጸው ኦክስፋም፥ ይህም በከፊል እየጨመረ ባለው የአሜሪካ የአክሲዮን ገበያ መነቃቃት መሆኑን ጠቁሟል።
በዚህ ፍጥነት ከቀጠለም በሚቀጥሉት አስር ዓመታት 1 ትሪሊየን ዶላር ሃብት የሚያፈሩ ቱጃሮች እንደሚኖሩ ግምቴ ነው ብሏል ድርጅቱ በሪፖርቱ፡፡
የኦክስፋም ከፍተኛ የፖሊሲ መሪ ሬቤካ ሪዴል በሰጡት አስተያየት ከልክ ያለፈ ኢ-እኩልነት መሞገስ የለበትም ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የቢሊየነር መደብ ደረጃ በእጅጉ በማደጉ ወደ 2 ሺህ 770 የሚጠጉ ሰዎች ሲደርስ፤ ሃብታቸው በ2 ነጥብ 1 ትሪሊየን ዶላር ተመንድጓል ነው የተባለው፡፡
የዓለም ባንክ መረጃን ጠቅሶ ኦክስፋም ባወጣው ሪፖርቱ በፈረንጆቹ 1990 በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ተመሳሳይ መሆኑ ዓለም ፍትሃዊ ያለመሆኗ ጉዳይ ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ ነው የሚለውን ያሳያል አስብሎታል፡፡