ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ከባቢን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ከባቢን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኗን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
69ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ሀገራት የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
“የአየር ንብረት አገልግሎት፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍተቶችን በጋራ ለመሙላት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ በሚገኘው ፎረም የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ ሞቱማ መቃሳ በወቅቱ እንዳሉት፥ የአየር ንብረት ትንበያ በአየር ንብረት ለውጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ያስችላል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ጫና ተጠቂ የሆነው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የአየር ንብረት ትንበያን ማጠናከር ይጠበቅበታል ብለዋል።
ለዚህም የኢጋድ አባል ሀገራትና አጋር አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ አስፈላጊውን የአየር ትንበያ በመስጠት በተለያዩ ዘርፎች ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መቀነስ ተችሏል ሲሉ አብራርተዋል።
የአየር ትንበያ ተደራሽነትን ለማዘመንና ለማስፋፋትም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በመላኩ ገድፍ