የሺህ ጋብቻ የፊታችን እሁድ ይከናወናል
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2017 የሺህ ጋብቻ “ቤተሰብን መመስረት ሀገርን መገንባት ነው”በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን እሁድ እንደሚከናወን ተገለጸ።
የዘንድሮው የሺህ ጋብቻ ከኢትዮጵያ አልፎ ከ43 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ጥንዶች ለመሳተፍ መመዝገባቸው ተገልጿል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊዛ አልማሃዲን÷ የሺህ ጋብቻ ባህል እና እሴቶቻችን ጎልተው እንዲወጡ የሚያግዝ ማህበራዊ ክንውን ነው ብለዋል።
የዘንድሮው የሺህ ጋብቻ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑንና የአፍሪካ ሀገራት ጥንዶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ የፈጠረው ውበት ለዘንድሮው የሺህ ጋብቻ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡
በዘንድሮው የሺህ ጋብቻ መርሐ ግብር ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ አዲስ የሰርግ ሙዚቃ ቪዲዮ መዘጋጀቱንም አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።
በቅድስት ብርሃኑ