325 ሺህ ሊትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር ውሏል – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 325 ሺህ ሊትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
“በጥራት ወደ ተሳለጠ የንግድ ስርዓት” በሚል መሪ ሀሳብ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሉት፥ ባለፉት ስድስት ወራት በወጪ ንግድ ዘርፍ ወደ 3 ነጥብ 28 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
ለሀገር ኩራት የሚሆነው የጥራት መንደር ኢትዮጵያን በሚወክልና በሚያስደንቅ ደረጃ ተገንብቶ መጠናቀቁንም ጠቅሰዋል።
በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አሰጣጥ ለንግድ ስርዓት ምቹ እንዲሆን በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በስድስት ወራት ከ2 ሚሊየን 50 ሺህ በላይ የንግድና ምዘገባ ፍቃድ አገልግሎት መሰጠቱንም አንስተዋል፡፡
በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 325 ሺህ ሊትር ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉንና ኩባንያዎች 116 ሚሊየን ብር እንዲቀጡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የሲሚንቶ ግብይት ላይ በተወሰደ የአሰራር ሰርዓት ማሻሻያ የተረጋጋ አቅርቦትና ግብይት እንዲኖር በመደረጉ ዋጋው በግማሽ ሲቀንስ፥ በጥቂት ነጋዴዎች ተይዞ የነበረው የጨው ግብይት በፍትሃዊነት ለሁሉም ክፍት እንዲሆን መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ተቋርጦ ከነበረበት ምዕራፍ በማውጣት ወደ ንቁ ድርድር አውድ መገባቱንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ለቀጣይ 5ኛ ዙር ድርድርም ብቃት ያላቸውን ሙያተኞችን በማደራጀት በቂ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡