Fana: At a Speed of Life!

ኮንኮርድ ሲታወስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በእንግሊዝ እና ፈረንሳይ መንግስታት ትብብር ለየት ባለ ንድፍ የተሰራው ኮንኮርድ የተባለ ሱፐርሶኒክ የመንገደኞች አውሮፕላን ተጓዦችን ጭኖ የመጀመሪያ በረራውን ያደረገው የዛሬ 49 ዓመት በ1976 በዛሬዋ ዕለት ነበር።

በታሪክ እጅግ ፈጣኑ የተባለው የመንገደኞች አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራውን ያደረገው ከለንደን ወደ ባህሬን እና ከፈረንሳይ ሪዮ ዲጀኔሮ በተመሳሳይ ቀን መሆኑ በታሪክ ተመዝግቧል።

ኮንኮርድ በአውሮፓዊያኑ 1996 በታሪክ እጅግ ፈጣኑን በረራ ከለንደን ኒውዮርክ ያደረገ ሲሆን አውሮፕላኑ በአሁኖቹ ዘመናዊ አውሮፕላኖች አንኳ በአማካይ 7 ሰዓት የሚፈጀውን በረራ፣ 2 ሰዓት ከ52 ደቂቃ ከ59 ሰኮንድ እንደፈጀበት ተገልጿል። 2 ሺህ 179 ኪሎ ሜትር በሰዓት ይምዘገዘግ እንደነበርም ነው የተገለጸው።

ኮንኮርድ የመጨረሻ በረራውን ያደረገው እ.ኤ.አ ኅዳር 26 ቀን 2003 ሲሆን የብሪቲሽ ኤርወይስ ንብረት የሆነው አውሮፕላኑ ከኒውዮርክ ተነስቶ ለንደን በሚገኘው ሂትሮው አውሮፕላን ማረፊያ አርፎ ነበር፡፡

በወቅቱ ሚዲያዎች በአውሮፕላን ማረፊያው በመገኘት ታሪካዊውን የአቪዬሽን ክስተቱን ሰፊ የዘገባ ሽፋን ሰጥተውት እንደነበርም ይጠቀሳል።

የዓለም ላይ 18 የሚሆኑ አየር መንገዶች ኮንኮርድ አውሮፕላን እንዲሰራላቸው ቢያዙም የብሪቲሽ ኤርወይስ እና ኤር ፍራንስ ብቻ ናቸው ጥቅም ላይ ያዋሉት፡፡

ኩባንያው ባጠቃላይ 20 አውሮፕላኖችን ያመረተ ሲሆን 14 ያህሉ መንገደኞችን ለማጓጓዝ የዋሉ ሲሆን ቀሪዎቹ ለናሙናና ለሙከራ በረራ የዋሉ ናቸው። በአሁኑ ወቅት 18 አውሮፕላኖች በተለያዬ አገራት ሙዚዬም ውስጥ ለዕይታ ተቀምጠዋል።

ኮንኮርድ ከአቪዬሽን ዓለም የተሰናበተው አውሮፕላኖቹ በስራ ላይ እንዲቆዩ ለማድርግ ከፍተኛ ወጭ መጠየቃቸው እንደ ምክንያት ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ ኮንኮርድ ሲነሳና ሲያርፍ የህንፃ መስኮቶችን የሚያርገፈግፍ ከፍተኛ የሆነ ድምፅ የሚፈጥር ሲሆን በድምፅ መለኪያ እስከ 110 ዴሲቢልስ ይደርሳል ተብሏል፡፡ ይህ ድምፅ በቅርብ አካባቢ ከሚፈጠር ከፍተኛ የነጎድጓድ ድምፅ ጋር የሚቀራረብ ነው፡፡

ኮንኮርድ በአንድ ጊዜ ከ98 እስከ 128 መንገደኞችንና ከ2 ቶን በላይ ዕቃዎችን ጭኖ መብረር ይችል እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከኮንኮርድ ጋር በተያያዘ ሌላው አስደናቂ ነገር ፍሬድ ፊን የተባለ እንግሊዛዊ ከለንደን አሜሪካ 718 ጊዜ በኮንኮርድ አውሮፕላን በመመላለስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡ ሲምፕሊፍላንግ ዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 25 ቀን 2000 የበረራ ቁጥሩ 4590 የሆነ የኤር ፍራንስ ኮንኮርድ አውሮፕላን ከፓሪስ ወደ ኒውዮርክ ለመብረር ሲያኮበኩብ ብረት ተፈናጥሮ የነዳጅ ጋኑ በእሳት ተያይዞ በመከስከሱ 109 ተሳፋሪዎች እና መሬት ላይ ለነበሩ 4 ሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት መሆኑ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.