በኢትዮጵያ ለዘመናት የነበረውን የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ሥርዓት ተዘርግቷል -ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለዘመናት የነበረውን የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ሥርዓት ተዘርግቷል ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር)÷ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና አጠቃላይ ለውጡን ተከትሎ በተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት የነበረው የፖለቲካ አካሄድ በሀገሪቱ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዳይገነባ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አንስተዋል።
የጠላትና የወዳጅ በሚል የተቃኘው የፖለቲካ ባህል፤ ከውይይትና ንግግር ይልቅ ለችግሮች የኃይል አማራጭን መከተል ስለነበር በሀገሪቱ የፖለቲካ ስብራት ማስከተሉን አስታውሰዋል።
በተለይም የፖለቲካ ተዋንያን ህዝቡን ከማቀራረብ ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮረ አካሄድን በመከተላቸው ለውስብስብ ችግር መዳረጉን ነው የተናገሩት።
በቀደሙት ሥርዓቶች ከውጭ ተቀድተው ተግባራዊ የተደረጉት የሊብራሊዝምና የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ለኢትዮጵያ በሚሆን ማልኩ ባለመቃኘቱ የዴሞክራሲ ስርዓት መፍጠር አለመቻሉን አንስተዋል።
የዋልታ ረገጥ እሳቤና የነጠላ ትርክት አካሄድን ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ ጥርጣሬና ልዩነትን ለማስፋት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አካታችና ሁሉንም አሳታፊ ሆኖ የተመሰረተው ብልጽግና ፓርቲ አሰባሳቢ ትርክትን የመፍጠርና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት የመገንባት ስራ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ስብራት በመጠገንና ለዘመናት የነበረውን የዴሞክራሲ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ሥርዓት በመዘርጋት ፓርቲው በተጠናከረ መልኩ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የፖለቲካ ሥርዓቱን ለመቀየር ፓርቲው ህብረብሄራዊ የሆነ ፓርቲ ሆኖ መመስረቱን ጠቁመው÷ ለዚህም የተደረጉ የፖለቲካ ሪፎርሞች ሁነኛ ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ህብረብሄራዊነት ታሳቢ ያደረጉ ሁሉን አቀፍ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ ተግባራዊ የተደረገው የመሃል የፖለቲካ እሳቤም አካታችና ሁሉንም አሳታፊ ባደረገ መልኩ ቀጥሏል ብለዋል።