ባለሃብቱን በመግደል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አቶ ቢረሳው ምናለ ፈንታ የተባሉትን ባለሃብት በመግደል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
አቶ ቢረሳው ምናለ ፈንታ የተባሉት እና ነዋሪነታቸው ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው አትሌቶች መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት ባለሃበቱ ታሕሳስ 21 ቀን 2017 ዓም በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ፖሊስ የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ በወንጀሉ ስፍራ ፈጥኖ በመድረስ የወንጀል ፈፃሚውን ማንነት ለማወቅና በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል፡፡
ከወንጀሉ ጀርባ ያሉ ግለሰቦችን ማንነትና ምንነት ለመለየት በተከናወነ የክትትል ስራ ወንጀሉን በመፈፀም የተጠረጠሩትን መኮንን ይዋል ይፍሩ እና አብዩ አይተነው ፈንታ የተባሉ ግለሰቦችን ጨምሮ ለወንጀሉ መፈፀም አካባቢውን በመቆጣጠር ተሳትፎ የነበረውን አቶ ወርቁ መለሰ ካሴ የተባለ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
ሦስቱም ተጠርጣሪዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት በጌዴኦ ዞን ይርጋ ጨፌ ከተማ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን÷ ግለሰቦቹ ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡