ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ የተተገበሩ ሪፎርሞች አካታችነትን እያረጋገጡ ነው – ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ በመንግስት የተወሰዱ ርምጃዎች ማህበራዊ አካታችነትን እያረጋገጡ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለፁ።
ሚኒስትሯ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም አዘጋጅነት በሚቀርበው ‘ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ’ ፕሮግራም ላይ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ከማህበራዊ አካታችነት አኳያ በነበራቸው ሚና ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው ሁለንተናዊ ብልጽግና ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ አንድምታዎች እንዳሉት ጠቅሰዋል።
ሁለንተናዊ ብልጽግና ደስተኛ ሕይወት፣ ማህበራዊ ዋስትና የማረጋገጥ፣ ክብር እና መሻትን ዕውን የማድረግ፣ በምቹና ተስማሚ አካባቢ የመኖር፣ አካታችነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥና መሰል ጽንሰ ሃሳቦችን እንደሚያቅፍ አብራርተዋል።
ከዚህ አካያ ባለፉት ዓመታት በተወሰዱ ርምጃዎች በሁሉም መስኮች አካታችና አሳታፊ ዕድገት በማስመዝገብ ማህበራዊ አካታችነትን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
ለዚህ ስኬት ዕውን መሆን መንግስት የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችን ቀይሶ መተግበሩን አውስተው፤ ማሻሻያዎቹ ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።
ከድህነት አዙሪት ለመላቀቅ የሀገርን ጸጋ የማየትና አቅምን አሟጦ በመጠቀም እመርታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ ለአብነትም ጥራት ያለው የጤና እና የትምህርት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የፖሊሲ ርምጃዎች ተተግብረዋል ብለዋል።
በአካታች ፋይናንስ ረገድም ከገጠር እስከ ከተማ አካታች የፋይናንስ ስርዓት ለመዘረጋት የተሄደውን ርቀት አውስተው፤ በድህነት ቅነሳ ረገድ ሰው ተኮር ፖሊሲዎች በመቅረፅ ዜጎች ከድህነት ተላቀው የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋግጡ አስቻይ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ማሳያዎችን በመጥቀስ አስረድተው፤ የኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑትን ጨምሮ አንድ ቢሊዮን ኩንታል ሰብል ምርት መመረቱን አንስተዋል።
በተለይም የስንዴ ልማት ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ ያደረገና እንደ ሀገር ራስን ያስቻለ ብቻ ሳይሆን ስንዴ ወደ ውጭ መላክ የተበሰረበት ስኬት መመዝገቡን አውስተዋል በማለት የዘገበው ኢዜአ ነው።
የግብርና ፖሊሲዎች በቴክኖሎጂ በታዘገ አነስተኛ መስኖ፣ በከተማ ግብርና፣ በኩታገጠም እርሻና መሰል መርሀ ግብሮችን በመተግበር የአምራቾች ሕይወትና ኑሮ እንዲለወጥ ያስቻሉ እንደሆኑም ገልጸዋል።
ይህም የምግብ ዋስትና እና ስርዓተ ምግብ ሽግግርን በማረጋገጥ ወደ ሁለንተናዊ ብልጸግና የሚያሸጋገር ወሳኝ እርምጃ እንደነበር ነው የጠቀሱት።
በሰብል ምርታማነት ብቻ ስርዓተ ምግብን ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቅሰው፤ በዚህም የእንስሳት ሀብትን በማመዘንና ምርታማነትን በመጨመር የአመጋግብ ስርዓትን ማሻሻል እንደሚያሻ ጠቁመዋል።
በዚህም በማር፣ በስጋ፣ በወተትና በእንቁላል ምርታማነት በመጨመር ስርዓተ ምግብን ለመለወጥ የተተገበረውን የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ውጤታማነት ጠቅሰዋል።
በስርዓተ ጾታ፣ በከተማ ቤቶች ልማት፣ በመሰረተ ልማት፣ በዲጂታል ኢኮኖሚና በፋይናንት ተቋማት በኩል የተወሰዱ ሪፎርሞችም ማህበራዊ አካታችነት ያረጋገጡና የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት ስለመጣላቸው አንስተዋል።