የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከዋንኮ ኢታሊ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከጣሊያኑ ዋንኮ ኢታሊ ኩባንያ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱ ኮርፖሬሽኑን ሕንጻዎችን በፍጥነትና በጥራት ለመገንባት የሚያስችል የግንባታ ቴክኖሎጂ ባለቤት ያደርገዋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
በተጨማሪም የመኖሪያ ቤት አሰራር ስልትን የሚያዘምን ግዙፍ የተገጣጣሚ ቤቶች ፋብሪካ ተከላን ለማከናወን የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የግንባታ ቴክኖሎጂው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማዘመን እያደረገ ያለውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዝ መሆኑም ተነስቷል፡፡
ቴክኖሎጂው በቀን አንድ የሕንጻ ወለል መገንባት የሚያስችል ሲሆን÷ ቪላ ቤትን ጨምሮ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች በአጭር ጊዜ መገንባት የሚያስችል ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል በዚህ ወቅት÷ ኮርፖሬሽኑ ጊዜን ፣ፍጥነትንና ውጤታማ የበጀት አጠቃቀም መርህን በቀላሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፋብሪካው ግንባታ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ክፍለከተማ ገላን አካባቢ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ 10 ሄክታር ይዞታ ላይ የሚገነባ ነው መባሉን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡