የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ ከሩሲያ አቻቸው ጋር በዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ዢንፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ጉዳዮች የጋራ ጥቅም አስመልክተው በበይነ-መረብ ተወያይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ÷ ፑቲንና ዢንፒንግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አንስቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በፈረንጆቹ 2024 75ኛውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማክበራቸውን ያመላከተው መግለጫ÷ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በዚሁ ዓመት ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ያደረጓቸውን ሦስት ውይይቶችና የደረሱባቸውንም የጋራ ግንዛቤዎች አስታውሷል።
ዘላቂ የመልካም ጉርብትና እና የወዳጅነት መንፈስን ያማከለ የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ ሁሉን አቀፍ ስልታዊና የጋራ ተጠቃሚነት ያለው ትብብር መታየቱም ተገልጿል።
እንደ የተባበሩት መንግስታት፣ የሻንጋይ የትብብር ድርጅት (ኤስ ሲ ኦ) እና ብሪክስ ባሉ ባለ ብዙ ወገን መድረኮች ለዓለም አቀፍ አስተዳደር ስርዓት ሪፎርምና ልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳደረገም ነው ፕሬዚዳንት ዢንፒንግ የገለጹት፡፡
ፕሬዝዳንቱ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ለመስራት እና የቻይና- ሩሲያ ግንኙነትን ወደ ላቀ ከፍታ ለማሳደግ፣ የሁለቱንም ሀገራት ልማትና ብልጽግና ለማሳደግ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትህ እንዲሰፍን ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት አብራርተዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በማጠናከር እርስ በርስ እንዲደጋገፉና ህጋዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ተግባራዊ ትብብርን ከማጠናከር አንፃር የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ማጎልበትና ማስፋት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል ፕሬዚዳንቱ።
ቻይና እና ሩሲያ የብሪክስ ትብብርን ይበልጥ በማሳደግ የግሎባል ደቡብ ትብብር ላይ አዲስ ምዕራፍ ለመጻፍ በአንድነት መስራት እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ሩሲያ እና ቻይና ሁልጊዜ እንደሚተማመኑ፣ እንደሚደጋገፉ እና አንዱ ሌላውን በእኩል እንደሚመለከት ጠቁመው ፥ የሁለቱም ህዝቦች ጥቅም የሚያስከብር የሁለትዮሽ ትብብር በዓለም አቀፍ መልክዓ ምድር ላይ ለውጥ ለማምጣት የማያስችል ሆኖ መቆየቱን መግለጻቸውን አስታውሰዋል።
ሩሲያ ከቻይና ጋር በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ትብብሯን ለማጠናከር እና ለዓለም ሰላም እና ልማት በጎ ሚና ለመጫወት ትኩረት ታደርጋለች ብሏል ኤምባሲው በላከልን መግለጫ፡፡
ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ፥ በፈረንጆቹ 2025 ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል መስማማታቸውም ተነግሯል።