በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የጎላ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች እና ኢንቨስተሮች ክፍት መደረጉ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ድርሻው የጎላ መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሙዓለ ንዋይ (ሃብት) የሚፈስባቸውን ሰነዶች ወይም ኢንቨስትመንቶችን እንደ ባለቤትነት የሚረጋገጥበት የሰነዶች ገበያ ሲሆን፤ በአብዛኛው አክሲዮን፣ የመንግስት ቦንድ፣ የግምጃ ቤት ሰነድ፣ የኩባንያዎች ቦንድ እና ሌሎች ቦንዶች ወደ ማዕከላዊ ቦታ መጥተው የሚገበያዩበት መድረክ ነው፡፡
ዘርፉ ለውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች፣ ኢንቨስተሮች እና ደላሎች ክፍት መሆኑን ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
የተለያዩ የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በተለያየ ጊዜ መጥተው ጉብኝት አድርገዋል፤ እኛም ሌሎች ገበያዎች ላይ በመሄድ የማስተዋወቅ ስራ ሰርተናል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች፣ ኢንቨስተሮች እና ደላላች ክፍት መደረጉን ጠቁመዋል።
ይህም የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ፣ ዘርፉን በሀገር ውስጥ በስፋት ለማላመድ፣ የሰው ሃይል እና የቴክኖሎጂ ትውውቅን ለማፋጠን ድርሻው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የህግ ማዕቀፍ ከሌሎች ሀገራት ጋር የተጣጣመ እና ለሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች ምቹ ሆኖ መቀረጹን ጠቅሰው፤ በዚህም ሶስት የሚሆኑ የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮችም ቢሮ ይከፍታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት ያለው የውጭ ተዋንያን እንደማንኛውም የውጭ ኢንቨስትመንት በኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኩል አስፈላጊውን መስፈርት አሟቶ ገበያውን መቀላቀል እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው