Fana: At a Speed of Life!

በለውጡ ዓመታት በመሰረተ ልማት አቅርቦት ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ ዓመታት በመሰረተ ልማት አቅርቦት ዘርፍ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

ከፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ በኋላ በመሰረተ ልማት ዘርፍ በተቀመጡ አቅጣጫዎች በተከናወኑ ተግባራት እና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፤ ከ1996 እስከ 2012 ዓ.ም 380 ሺህ ቤቶች ብቻ መገንባታቸውን አስታውሰዋል።

ከለውጡ በኋላ በቤት ልማት ፕሮግራም ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በፕሮግራሙ በህብረት ሥራ ማህበራትና በሪል ስቴት ጭምር የግልና የመንግሥት አጋርነት መርሃ ግብሮችን በመንደፍ መከናወኑንም አብራርተዋል።

በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በቤት ልማትና አቅርቦት ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ከተያዘው እቅድ አኳያ የተገኘው ውጤት አበረታች ቢሆንም ካለው የህዝብ ፍላጎት አንፃር የበለጠ መሥራት የሚጠይቅ ይሆናልም ነው ያሉት።

በኮሪደር ልማትም ከደረጃ በታች ሆነው የተገነቡ አካባቢዎችን በጥራት በመገንባት እንዲሁም ለመኖሪያ ምቹ አካባቢዎችን በመፍጠር ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በከተሞች 74 በመቶ ግንባታዎች ከደረጃ በታች መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ የኮሪደር ልማት ስራው የከተሞችን ጥራትና ደረጃ እያሻሻለ ይገኛል ነው ያሉት።

የመንገድ ልማት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተው፤ ለውጡን ተከትሎ በተዘረጋው ውጤታማ አሰራር 18 ሺህ 790 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ መገንባቱን በአብነት ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የመንገድ ሽፋኑ 171 ሺህ 174 ኪሎ ሜትር መድረሱንም ነው የተናገሩት።

በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ዲጅታላይዝ በማድረግ እንዲሁም ልማታዊ የምግብ ዋስትን በማረጋገጥ ረገድም አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.