በኦሮሚያ ክልል 94 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት 6 ወራት 94 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ረመዳን ዋሪዮ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት 200 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም በግማሽ ዓመቱ ከተለያዩ ገቢዎች 104 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 94 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ36 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የግብር አሰባሰብ ሒደቱን ለማሳለጥ የተለያዩ ስተራቴጂዎችን በመንደፍ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉንም ምክትል ሃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
በግብር ከፋዮች ላይ አላስፈላጊ እንግልት በፈጠሩ ግለሰቦች ላይ የተለያዩ ርምጃዎች መወሰዳቸውን አመልክተዋል፡፡
በፀሃይ ጉሉማ