Fana: At a Speed of Life!

በርካታ ፍልስጤማውያን ወደ ቀያቸው መመለስ ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እስራኤል እና ሃማስ የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜን ጋዛ ማቅናት ጀምረዋል፡፡

እስራኤል እና ሃማስ የደረሱት ታጋቾችን የመለዋወጥ ስምምነት ተከትሎ ነው ፍልስጤማውያኑ ተፈናቃዮች እስራኤል ተቆጣጥራው በነበረው ኔትዛሪም ኮሪደር በኩል ወደ ሰሜን ጋዛ እየሄዱ ያሉት፡፡

ፍልስጤማውያኑ በእግር እና በተሽከርካሪ ወደ ሰሜን ጋዛ እንዲገቡ መፍቀዷን የገለጸችው እስራኤል እስከ አሁን ድረስ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ወደ ከተማቸው እየገቡ መሆናቸውን አስታውቃለች፡፡

ወደ ከተማቸው መመለሳቸው ደስታን ቢፈጥርላቸውም በነበረው የከፋ ጦርነት ምክንያት ቤትና ንብረታቸውን የማግኘት ዕድል እንደማይኖራቸው ፍልስጤማውያኑ ገልጸዋል፡፡

ቢቢሲ ያነጋገረው የ42 ዓመት ዕድሜ ያለው ፍልስጤማዊ ኒርመን ሙሳቤህ “ወዳደኩበት ቀየ መመለስ እፈልጋለሁ፤ ምንም እንኳን ቤቴ ቢኖርም ባይኖርም” ብሏል፡፡

ተፈናቃዮቹ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ወደ ጋዛ እንዲመለሱ ከስምምነት ተደርሶ የነበር ቢሆንም÷ ሃማስ የ28 ዓመቷን እስራኤላዊ ታጋች ባለመልቀቁ ምክንያት መዘግየታቸው ተነግሯል፡፡

ይሁን እንጂ ታጋቿ የፊታችን ሐሙስ ለቀይ መስቀል ማኅበር ተላልፋ እንድትሰጥ መግባባት ላይ መደረሱን ተከትሎ ፍልስጤማውያኑ ከሁለት ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ ጋዛ መግባት ጀምረዋል፡፡

በአቤል ንዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.