በአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ የከፍተኛ ደረጃ ስብሰባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ የከፍተኛ ደረጃ ስብሰባ በኬኒያ ናይሮቢ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ዛሬ እና ነገ የሚካሄደው ስብሰባው በአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ በተለይም በህብረቱ ዘላቂ ፋይናንስ እና የስራ መዋቅር ማሻሻያ እንዲሁም ህብረቱ ለአህጉራዊ ፈተናዎች መፍትሄ በመስጠት ግቦቹን ማሳካት የሚችልበት አቅም መገንባት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ የከፍተኛ ደረጃ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ሲሆን፥ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች በስብሰባው ላይ እየተሳተፉ መሆኑም ተጠቁሟል።
የኬኒያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እንዳሉት፥ የአፍሪካ መሪዎች በስብሰባው መገኘታችሁ የአህጉሪቱን የወደፊት ዕጣ አስመልክተን ለመምከር ነው ብለዋል፡፡
አህጉሪቱ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ችግሮች የገጠሟት ጊዜ ላይ ብንሆንም አሁንም እድሎች አሉ ሲሉ አንስተዋል፡፡
የአፍሪካን አቅም የምንገልጥበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ያሉት ፕሬዚዳንት ሩቶ፥ ለዚህም ፖለቲካዊ ፈቃደኝነትና አህጉሪቱን ለማበልጸግ ከልብ የሆነ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት ባደረጉት ንግግር፥ የህብረቱ በጀት በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም በቂ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
ሪፎርም ቀላል ባይሆንም ለአፍሪካ ብልጽግና ግን የግድ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ አህጉሪቱ ለምትጋፈጣቸው ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ግቦቹ ላይ ለመድረስ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ እንዲቋቋም በአፍሪካ መሪዎች የተወሰነው በፈረንጆቹ 2016 መሆኑ ይታወሳል፡፡
በመሰረት አወቀ