Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ የካንሰር መከላከያ ክትባት ሙከራ ልታካሂድ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሩሲያ የካንሰር መከላከያ ክትባት ሙከራ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት አጋማሽ ላይ እንደምታካሂድ አስታውቃለች፡፡

የሩሲያ ተመራማሪዎች ለበርካታ ዓመታት ሁሉንም የካንሰር ዓይነቶች ለመከላከል የሚውል ክትባት ለዓለም ለማበርከት ሲሰሩ መቆየታቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህም ከዓመት በፊት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው የካንሰር መከላከያ ክትባት ለማግኘት መቃረቧን መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

በሞስኮ በፊውቸር ቴክኖሎጂ ፎረም ላይ ስለ ሩሲያ የሕክምና ሳይንስ ወቅታዊ ሁኔታ ያነሱት ፕሬዚዳንት ፑቲን፥ ካንሰርን አስቀድሞ በመለየትና በማከም ረገድ ከፍተኛ እምርታ መታየቱን ጠቁመው፤ይህም የካንሰርን የመዳን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም “ኦንኮ-ክትባት ተብለው የሚጠሩትን የካንሰር መከላከያ ክትባቶች እና የበሽታ መከላከያ መድሃኒቶች ለማግኘት ተቃርበናል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ከፈጠራዎቹ ውስጥ አንዱ በአንጎል ውስጥ ከተተከለ የሰውን የእይታ አቅም ወደነበረበት መመለስ የሚችል ልዩ ቺፕ ነው ያሉ ሲሆን፥ ቴክኖሎጂው በአሁኑ ጊዜ ክሊኒካዊ ሙከራዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ክትባቱ የሚሠራው አንድ የተወሰነ ሪቦናክሊክ አሲድን (አር ኤን ኤ) በቅደም ተከተል ወደ ሰውነት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ቅድመ-ክሊኒካዊ ሙከራዎች በመስከረም ወር መጠቃለላቸውን ያመላከተው የስፑትኒክ መረጃ ባለፈው ሕዳር ላይ በተደረገው የእንስሳት ላይ ሙከራ የእጢ መጠን 80 በመቶ እንደቀነሰ ማወቅ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ክትባቱ ይፋ ሲደረግም የሩሲያ ግኝት በመሆን ታሪክ እንደሚመዘግበው ፑቲን በወቅቱ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

ክትባቱ በጋማሌያ ማዕከል፣ በሄርሴን ኦንኮሎጂ ምርምር ኢንስቲትዩት እና በብሎኪን የካንሰር ምርምር ማዕከል በጋራ የተሰራ ነው ተብሏል።

በመሰረት አወቀ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.