Fana: At a Speed of Life!

በሮቦቶችና በሰው ልጆች የሚደረገው የሩጫ ውድድር

ሮቦቶች የሰው ልጆችን በሩጫ ውድድር የማሸነፍ አቅም ይኖራቸው ይሆን? በመጪው ሚያዝያ ወር ቁርጡ ይታወቃል።
በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዓለም ታዋቂ የሮቦቲክስ ኩባንያዎች ባዘጋጁት በደርዘን ከሚቆጠሩ ሰው መሰል ሮቦቶች ጋር የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ሊያደርጉ ቀን ተቆርጦለታል።
በመጭው ሚያዝያ ወር የሚካሄደው እና ለሰው ልጆችም ሆነ ለሮቦቶች አስደሳች ነው የተባለለትን ውድድር የቤጂንግ ኢኮኖሚ እና ቴክኖሎጂ ልማት ዲስትሪክት አዘጋጅቷል።
ቴስላ፣ ቦስተን ዳይናሚክስ እና 1Xን ጨምሮ ታላላቅ የሮቦቲክስ ኩባንያዎች የገነቧቸው በደርዘን የሚቆጠሩ ባለ ሁለት ፔዳል ወይም ሰው መሰል ሮቦቶች በውድድሩ ቋሚ ተሰላፊዎች ናቸው።
12ሺህ ሰዎች ደግሞ ብርቱ ፉክክር አድርገው ሮቦቶችን ለማሸነፍ በግማሽ ማራቶን ውድድሩ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ተሰላፊ ሮቦቶች የሰው ቅርጽ፣ ቢያንስ ከግማሽ እስከ 2 ሜትር ቁመት እና የመሮጥ ችሎታ ሊኖራቸው እንደሚገባ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
አሸናፊዎቹ ሰውም ይሁኑ ሮቦት እንደ አፈፃፀማቸው የገንዘብ ሽልማት ያገኛሉ ተብሏል።
የሮቦቶቹ ፍጥነት በሰዓት ከ8 እስከ 12 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስ ይገመታል። 21 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የግማሽ ማራቶን ውድድር በአንድ ሰዓት ተኩል ውስጥ ለማጠናቀቅ ደግሞ በአማካይ በሰዓት 14 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ያስፈልጋል። ይህ ለሮቦቶቹ ምናልባትም ፈተና ሊሆንባቸው ይችላል።
በተጨማሪም ሮቦቶችን የሚገጥማቸው የባትሪ ችግር ሲሆን የውድድሩ አዘጋጆች ግን በውድድሩ አጋማሽ ላይ ባትሪ መቀየር እንደሚፈቀድ አስታውቀዋል።
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር “ቲያንጎንግ” የተባለ በቻይና የተሰራ ባለ ሁለት ፔዳል ሮቦት በቤጂንግ ይዙዋንግ ግማሽ ማራቶን ላይ መሳተፉ ይታወሳል። ነገር ግን 100 ሜትሮችን ሮጦ ፎቶ ከመነሳት የዘለለ ልዩ አቅም አላሳየም ነበር።
ቲያንጎንግ በሚያዝያ በሚደረገው ውድድር እንደሚሰለፍም ታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.