ሐማስ 8 ታጋቾችን ለቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሐማስ በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት ሥምንት እስራኤላውያንና የታይ ዜጎችን መልቀቁ ተሰምቷል፡፡
በቴል አቪቭ በግዙፍ ስክሪን ታጋቾች ሲለቀቁ የተመለከቱ በርካታ እስራኤላውያን ደስታቸውን ሲገልጹ እንደነበር መመልከት ተችሏል፡፡
በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት እስራኤል ከእገታ ነጻ በሆኑት ምትክ 110 የፍልስጤም እስረኞችን ትለቃለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እስራኤል እና ሐማስ የሥድስት ሣምንት የእርቅ ስምምነት ሲያደርጉ ዛሬ የተደረገው የታጋቾች ልውውጥ ሦስተኛው ሲሆን፥ ይህም ሁለቱን አካላት የሚያሸማግሉ ጦርነቱን ያቆማል ብለው ተስፋ ያደረጉበት የሥምምነቱ አንድ አካል ነው።
በሥምምነቱ መሰረት ሐማስ በእስራኤል የታገቱ ከ1 ሺህ 500 በላይ ፍልስጤማውያንን ለማስለቀቅ በጋዛ ውስጥ ከቀሩት 97 ታጋቾች መካከል ቢያንስ 33ቱን ለመልቀቅ ወስኗል።
ሆኖም በመጪዎቹ ሣምንታት ይለቀቃሉ ተብሎ ከሚጠበቁት ቀሪ 25 ታጋቾች መካከል ስምንቱ በህይወት አለመኖራቸውን የሚያመለክት ዝርዝር ከሐማስ ማግኘታቸውን የእስራኤል ባለስልጣናት ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ ነው።