ጀርመን ሩሲያ ወደ ቡድን 7 አባል ሃገራት ዳግም እንድትመለስ የቀረበውን እቅድ ውድቅ አደረገች
አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ ወደ ቡድን 7 አባል ሃገራት ዳግም እንድትመለስ ያቀረቡትን እቅድ ውድቅ አደረገች፡፡
የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄኮ ማስ ሃገራቸው የትራምፕን ሃሳብ እንደማትቀበል ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር ሞስኮ ዳግም አባል ትሆን ዘንድ ሃሳብ አቅርበው ነበር፡፡
ይሁን እንጅ የእርሳቸው ሃሳብ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በተለይም በምስራቃዊ ዩክሬን እና የክሬሚያን ጉዳይ እስካልፈታች ድረስ የቡድን 7 አባል የመሆን እድል የላትምም ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይ ከሩሲያ ጋር ያለውን ግንኙነት “አስቸጋሪ” ሲሉ የገለጹት ሚኒስትሩ ሞስኮ ሶሪያን እና ሊቢያን ጨምሮ በዩክሬን ጉዳይ ሰላም ማምጣት እንዳለባት አስረድተዋል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ወደ ቡድን 7 አባል ሃገራት ዳግም የመመለስ ፍላጎት እንደሌላት ገልጻለች፡፡
የቀድሞው የቡድን 8 አባል ሃገራት ጥምረት ሩሲያ ከጥምረቱ ከወጣች በኋላ የ7 አባል ሃገራት ጥምረት ሆኗል፡፡
ሩሲያ በፈረንጆቹ 2014 የዩክሬኗን ክሬሚያን መጠቅለሏን ተከትሎ ከአባልነት መውጣቷም የሚታወስ ነው፡፡
ሞስኮ ከቡድን 7 አባል ሃገራት አባልነት ብትወጣም ሰፊ በሆነው የቡድን 20 አባል ሃገራት ውስጥ ትገኛለች፡፡
ምንጭ፣ ሬውተርስ