የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ”ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ ሐሳብ ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ተጠናቀቀ፡፡
ጉባዔው የተጠናቀቀው ባለሥምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ነው፡፡
ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፕሬዚዳንትነት እንዲሁም አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና አቶ አደም ፋራህ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ ጉባዔው በድጋሚ መርጧል፡፡
ሕዝቡን ያሳተፉ ዘርፈ-ብዙ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ፓርቲው ያረጋገጠው፡፡
ፓርቲው የሚዲያ ነጻነት እንዲጠበቅ እንደሚሠራ እንዲሁም አፍራሽ ተልዕኮን ያነገቡ አካላትን አበክሮ እንደሚታገል የጉባዔውን መጠናቀቅ ተከትሎ በቀረበው የአቋም መግለጫ ላይ አስገንዝቧል፡፡
የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተመላከተው፡፡
ሁልጊዜም ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት፤ ግጭትን ለማስቀረት ሁሉም የፓርቲው አመራር እና አባላት በትጋት እንዲሠሩ አቅጣጫ መቀመጡ በአቋም መግለጫው ተገልጿል፡፡
በቀጣይ ጉባዔ ስንገናኝ ከተሰጠን በላይ ሠርተን እና ከሚጠበቅብን በላይ ፈጽመን ኢትዮጵያን በይበልጥ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና አሸጋግረን እንደሚሆን እናምናለን ብሏል ፓርቲው፡፡
በዮሐንስ ደርበው