Fana: At a Speed of Life!

17 ሺህ 400 የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማሕበረሰቡ ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 17 ሺህ 400 የቀድሞ ተዋጊዎች በተሃድሶ ሥልጠና ሒደት አልፈው ወደ ማሕበረሰቡ መቀላቀላቸውን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን እንደገለጹት÷ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማሕበረሰቡ የመቀላቀልና መልሶ የማቋቋም ሥራ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ከትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና አፋር ክልሎች ጋር በቅንጅት መሰራቱን ጠቁመው÷ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በተለይም ተቋማዊ የመፈጸም አቅምን በማጎልበት በፕሮግራሙ የመጀመሪያ ዙር ተሳታፊ ለሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ማስፈጸሚያ ሃብት ከመንግስትና ለጋሽ አካላት መገኘቱ አበረታች እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሚሽኑ ሥራዎች ለዘላቂ ሰላም ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ መግለጻቸውንም የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

የማዕከላት ጥገና መጓተት፣ ለመልሶ ማቋቋም ሥራ ትግበራ የሚሆን በቂ ሃብት አለመገኘት እና በአንዳንድ ክልሎች ለሥራው ምቹ ያልሆነ የፖለቲካ አውድ መኖርን በተግዳሮትነት አንስተዋል፡፡

ከሕዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮም ከትግራይ፣ አፋር፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከ17 ሺህ 400 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች በተሃድሶ ሒደት አልፈው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.