ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራች ነው – ዶ/ር መቅደስ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጄኔቫ እየተካሄደ በሚገኘው 156ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡
ዶ/ር መቅደስ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ፥ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ደረጃ ጤና አጠባበቅ፣ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት እንዲሁም በጤና ፋይናንስ ላይ በትኩረት እየሰራች ነው፡፡
ኢትዮጵያ አጠቃላይ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን በማሳደግ ረገድ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው÷የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል ትብብርና አጋርነት እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በጤና ላይ ዓለም አቀፍ ደንቦችና ደረጃዎችን በማውጣት ያለውን ከፍተኛ ሚና አጽንዖት የሰጡት ሚኒስትሯ ፥ ለሀገራት የሚያደርገውን ድጋፍም እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ በተሻሻለው የዓለም አቀፍ የጤና ደንቦች ላይ የተገኙ ስኬቶችን ያደነቁት ሚኒስትሯ ፥ ሁሉም አባል ሀገራት የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኝ ስምምነትን በፈረንጆቹ ግንቦት 2025 እንዲያጠናቅቁ ጠይቀዋል።
ጉባዔው ከዛሬ ጀምሮ በፕሮግራሙ በጀት፣ ዘላቂ ፋይናንስ እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡