Fana: At a Speed of Life!

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ምባፔ በአጥቂነት ስፍራ ለመጫወት መቸገሩን ተናገረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ወጣቱ የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ክሊያን ምባፔ በአጥቂነት ስፍራ ለመጫወት መቸገሩን ፖርቹጋላዊው እግር ኳስ ኮኮብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ገለጸ።
ሮናልዶ ከኤል ክሪንጉይቶ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ባለፈው የውድድር ዘመን ቡድኑን ለተቀላቀለው ፈረንሳዊ እግር ኳስ ተጫዋች ምክር ለግሶታል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለምባፔ “እሱን ብሆን ልክ እንደ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አጥቂነት እጫወት ነበር” በማለት ራሱኑ ምሳሌ አድርጎ አቅርቧል።
የአጥቂነት ስፍራው ለምባፔ ትንሽ አስቸግሮታል ያለው ሮናልዶ “በቦታው እንደ አጥቂ ለመጫወት አላወቀበትም፣ ምክንያቱም የሱ ቦታ አይደለም” ሲል ተጫዋቹ በቅርብ ብቃቱን ለማሳዬት የተቸገረበትን ሁኔታ ጠቁሟል።
“በሪያል ማድሪድ ብሆን፣ በ9 ቁጥር ቦታ አንዴት መጫወት እንዳለበት አስተምረው ነበር” ያለው ሮናልዶ ቡድኑ ምባፔን ሊደግፈውና ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስቧል።
ምባፔ ለሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች የደስታ ምንጭ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም ያለው የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ፣ የሪያል ማድሪድ፣ የጁቬንቱስና የስፖርቲንግ አጥቂ “ይህን ልጅ ተንከባከቡት” ሲል ምክሩን ለግሷል።
ሮናልዶ እግር ኳስ ቡድን ለማሰልጠን ይፈልግ እንደሆን ተጠይቆ “እኔ ለአሰልጣኝነት? አይመስለኝም። ከተጫዋችነት የበለጠ ከባድ ነው፣ ምናልባት እግር ኳስ ቡድን ሊኖረኝ ይችላል” ሲል ተናግሯል።
ሪያል ማድሪድ በታሪክ ታላቁ እግር ኳስ ቡድን ነው ያለው የ39 ዓመቱ ሮናልዶ፣ “እኔ የምንጊዜውም የተሟላ ተጫዋች ነኝ። ክሪስቲያኖ ሙሉ ተጫዋች አይደለም ማለት ሐሰት ነው” ሲል ራሱን አሞካሽቷል።
በሳኡዲው አልናስር እየተጫተ የሚገኘው ሮናልዶ ስለ ሌላኛው የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ጁድ ቤሊንግሃም አስተያዬት ሰጥቷል።
“ጁድ በሊንግሃም ወጣትና ከፊቱ ብሩህ ጊዜ ይጠብቀዋል፣” ያለው ፖርቹጋላዊ “የዜነዲን ዚዳን አይነት አጨዋወት አለው” ሲል አድናቆቱን አክሏል።
የአምስት ጊዜ ባሎን ዶር አሸናፊው ሮናልዶ በቃለ መጠይቁ ስለ አሰለጣጠኑ፣ አመጋገቡ፣ ክበረ ወሰን ስለመስበር፣ ጫማ ስለመስቀል ወዘተ አንስቷል።
ተጫዋቹ ከተለያዩ እግር ኳስ ቡድኖች ጋር 5 የቻምፒዮንስ ሊግ፣ 4 የፊፋ ክለብ ወርልድ ካፕ፣ 2 የላሊጋ ጨምሮ 33 ዋንጫዎች ያሸነፈ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2016 አውሮፓ ዋንጫንና በ2019 የዩሮፓ ኔሽንስ ሊግ ዋንጫን አሸንፏል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.