Fana: At a Speed of Life!

ግለሰቦች የግል መረጃቸውን በመጠበቅ ከማንነት ስርቆት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግለሰቦች የግል መረጃቸውን በመጠበቅ ከማንነት ስርቆት (identity theft) ራሳቸውን እንዲጠብቁ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን አሳሰበ፡፡

 

የግለሰብ መረጃ  ስምን፣ መለያ ቁጥርን፣ የስልክ ቁጥርን፣ የኮምፒውተር አይፒ አድራሻን፣ የቦታ ዳታን፣የኦንላይን መለያን፣ አካላዊ፣ የጄኔቲክ፣ የአዕምሮ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ወይም የማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር ተያያዥ የሆኑ መለያዎችን ይይዛል፡፡

 

የግላዊነት መብት በሕገ መንግስቱ ውስጥ ዕውቅና ከተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች አንደኛው ሲሆን ይህ መብት በበርካታ ሀገራት ሕገመንግሥት እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ውስጥ የተካተተ መብት ነው።

 

አሁን ላይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘንድ የተለያዩ የመረጃ ስርቆቶች የሚፈጸሙ ሲሆን የግላዊነት መብትም ሲጣስ ይስተዋላል፡፡

 

የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚሊዮን ሀይለ ሚካኤል ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷በኢትዮጵያ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና በማህበራዊ ትስስር ገፆች የመረጃ ስርቆት ወንጀሎች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡

 

ለአብነትም በባንክ እና በሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የግለሰብ መረጃዎችን በማመሳሰል በርካታ ወንጀሎች እንደሚፈፀሙ አንስተዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ የኮምፒውተር እና የመረጃ ስርቆት ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችል አዋጅ ጸድቆ ወደ ስራ መግባቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ÷ አዋጁ ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲቀጡ ከማደረግ ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታ እንደማይችል ገልፀዋል፡፡

 

 

በመሆኑም ግለሰቦች እና የግለሰቦችን መረጃ የሚይዙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የግል መረጃዎችን በመጠበቅ የማንነት እና የመረጃ ስርቆትን ሊከላከሉ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡

 

የግለሰቦች መረጃ የሚጠበቅ ከሆነ ግለሰቦች በእለት ከእለት ህይዎታቸው ውስጥ በአገልገሎት ሰጪ ተቋማት ህጋዊ ግልጋሎት ማግኘት የሚችሉ መሆኑን እንዲሁም የመረጃ ስርቆት በሚፈፀምበት ጊዜ ሰዎችን በህግ ለመጠየቅ ያስችላል ብለዋል፡፡

 

በዚህ ረገድ ባለስልጣኑ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የግለሰብ መረጃን ለማስጠበቅ ግንዛቤ የማስጨበት ስራዎችን እያከነወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

 

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.