የእንስሳት በሽታ በዜጎች ጤናማ አኗኗር ላይ ያለውን ተጽዕኖ በመረዳት ችግሩን በጋራ መፍታት ይገባል-ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንስሳት በሽታ በእንስሳት ተዋፅዖ ውጤቶች ምርታማነትና በዜጎች ጤናማ አኗኗር ላይ ያለውን ቀጥተኛ ተጽዕኖ በመረዳት ችግሩን በጋራ ትብብር ልንሻገረው ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ 26ኛው የዓለም እንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ አስጀምረዋል።
ይህንን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስሰር ገፃቸው ÷በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በመኖ አቅርቦትና ጥራትን ለማሻሻል በሰተራው ስራ በንጥረ ነገረ የበለፀገ ምግብ በማምረት የአመጋገብ ስርዓትን ለማሻሻልና የእንስሳት ጤና እንዲጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡
እንደ አህጉር ፈተና የሆነውን የእንስሳት በሽታ ለመከላከልም ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን ከማቋቋም አንስቶ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት መከናወኑንም ገልፀዋል፡፡
የእንስሳት ሕክምና አገልግሎት እንዲጠናከር በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽኦ ንግድ ዘርፍ ያሉ የጤና አጠባበቅ ህግጋት መከበር ላይ እንደዚህ ያሉ ጉባኤዎች ከፍተኛ ሚና ስለሚኖራቸው ትብብሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡