Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኬንያ የሸኔ ታጣቂ ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ማካሄድ ጀመሩ

 

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያና ኬንያ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ማካሄድ መጀመራቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የኬንያ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ኑረዲን ሞሐመድ ሐጂ እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት የመከላከያ እና የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ተወያይተዋል።

በጋራ ምክክር መድረኩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በቀጣናዊ የጸጥታ እና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ማካሄድ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉትን ሽብርተኝነት፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች እና የመሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል ተግባራዊ መሆን የጀመረው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በዋናነት በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፈውን የሸኔ ታጣቂ ከሁለቱ ሀገራት ድንበሮች አካባቢ ለማስወገድ የሚረዳ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም የሁለቱ ሀገራት የደኅንነትና የጸጥታ አካላት በየድንበራቸው ውስጥ በሚገኙ የቡድኑ ካምፖች ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን እያካሄዱ እንደሚገኙ ነው የተገለጸው፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የኬንያ ብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው÷ የሸኔ ቡድን በሀገሪቱ የድንበር አካባቢ በመንቀሳቀስ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ ወንጀሎች ላይ ይሳተፋል፡፡

ቡድኑ በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ፣ የሰዎችና የማዕድን ንግድ እንዲሁም የጎሳ ግጭት በመቀስቀስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሀገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ሆኖ መቆየቱንም አንስቷል፡፡

በዚህም የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ መጠነ ሰፊ ኦፕሬሽን መካሄድ መጀመሩን ገልጾ÷ እስካሁን በተከናወኑ ኦፕሬሽኖች በታጣቂ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል ተብሏል፡፡

የተጀመረው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጠው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ የሸኔ ታጣቂ ቡድን የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመርገጥ በራሱ ላይ ጥፋት ቢያውጅም፤አሁንም የሰላም መንገዱ ዝግ አለመሆኑን አስገንዝቧል፡፡

ቀሪዎቹ የቡድኑ አባላትም የጥፋት መንገዱን በመተው የቀረበላቸውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ጥሪ መቅረቡንም የአገልግሎቱ መረጃ አያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.