ኢትዮጵያና ቼክ በዱር እንስሳት ጥበቃ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ በዱር እንስሳት ጥበቃ እና ምርምር ላይ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን በቼክ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ከቼክ ሪፐብሊክ የዱር እንስሳት ጥበቃ ኢንስቲትዩት አመራሮች ጋር ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ በዱር እንስሳት ጥበቃና ምርምር ዘርፍ በጋራ መስራት እንደሚያስችላቸው ተገልጿል፡፡
በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው የዱር እንስሳቶችን ከአደጋ በመከላከል ቁጥራቸው እንዲጨምር ለማስቻል በጥናት የተደገፈ ትብብር ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃና ሥነ-ምሕዳር አጠባበቅን በተመለከተ ከቼክ ሪፐብሊክ የአቅም ግንባታና ሌሎች የቴክኒክ ድጋፎችን እንድታገኝ የሚያግዝ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡