የታዳጊ ወጣቶች የስፖርት ምዘና ውድድር በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት”የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለአሸናፊ ሀገር” በሚል መሪ ሃሳብ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ምዘና ውድድር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ተጀምሯል።
በመርሐ ግብሩ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ ÷ስፖርት ለሀገራዊ ብልጽግና ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በመረዳት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለውጤታማነቱ የሚረዱ ሀገራዊ ጥናቶችን በማስጠናት የአደረጃጀት እና የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን ፣ ተከታታይነት ያለው ሳይንሳዊ ስልጠና በመስጠት በብቃታቸው ፣ በተክለ ሰውነታቸውና በፍላጎታቸው የላቀ ችሎታ ያላቸውን ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ይህ ውድድር የስፖርቱን ስብራት ለማስተካከል በጥናት ለሚጀመረዉ ከፍተኛ ሀገራዊ የንቅናቄ መድረክ ስኬት አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ፥ የተተኪ ስፖርተኞች እጥረትን ለመቅርፍ ይህ የምዘና ውድድር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለተከታታይ ስድስት አመታት ተቋርጦ የነበረው ይህ ውድድር ለ8ኛ ዙር ከጥር 27 እስከ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።
በውድድሩ ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉ ሲሆን ከ2 ሺህ 600 በላይ ተወዳዳሪዎች በ11 የውድድር ዓይነቶች ይሳተፋሉ።
በመለሰ ታደለ