አቶ አደም ፋራህ ከደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ዋና ፀሀፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ከደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ዋና ፀሀፊ ፒተር ላም ቦዝ ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ አደም ፋራህ የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ ጉባዔን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ዋና ፀሀፊ ፒተር ላም ቦዝ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን በማበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
በውይይታቸውም የሀገራቱን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ሊያሳድግ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጠናከርና የሁለቱን ህዝቦች ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት ቁርጠኛ ነው ሲሉም አቶ አደም ፋራህ አረጋግጠዋል።
ደቡብ ሱዳን ሁልጊዜም ቢሆን በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትሰለፍ እና ኢትዮጵያ ለምታደርገው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ያላቸውን አክብሮት ዋና ፀሀፊ ፒተር ላም ቦዝ በውይይቱ ወቅት መግለጻቸውም ተመላክቷል፡፡