የልማት አጋር ሀገራትና ድርጅቶችኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የልማት አጋር ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ገለጹ።
በኮፕ-29 ጉባኤ ቃል በተገቡ ሥራዎች ትግበራ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬትና የቀጣይ መርሃ ግብሮችን አስመልክቶ በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ስኬታማ ጥረት ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር፣ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም እና ለችግሮች የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የልማት አጋር ድርጅቶች ሚና ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ የአየር ንብረት እና የግብርና መሪ ኒና ሂሰን(ዶ/ር)÷እንግሊዝ በአፍሪካ ሀገራት በአየር ንብረትና ተፈጥሮ ጥበቃ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
በፎረሙ የሚቀርቡ ሃሳቦችም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የኖርዌይ ኤምባሲ የአየር ንብረት ለውጥ አማካሪ ሰለሞን ዘውዴ(ዶ/ር)÷ ሁለቱ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም በካርቦን ሽያጭና ደን ልማት ዘርፍ የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአካበቢና የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ስትራቴጂክ አጋርነት መሪ ሥራ አስፈፃሚ መንሡር ደሴ÷ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መከላከል ስምምነቶች እየተገበረች ነው ብለዋል።
በቀጣይ በብራዚል በሚካሄደው የኮፕ-30 ጉባኤም የኢትዮጵያንና አፍሪካን ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችሉ የትኩረት መስኮችን ለአጋር አካላት የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ አንደሚገኝ ማስረዳታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።