አሜሪካ ጋዛን መልሳ መገንባት ትፈልጋለች አሉ ፕሬዚዳንት ትራምፕ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
መሪዎቹ ውይይታቸውን አስመልክተው በነጩ ቤተ-መንግስት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ÷ አሜሪካ ጋዛን በመረከብ ወደቀደመ ሁኔታዋ በመመለስ እንደገና መገንባት እንደምትሻ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ሀገራቸው በጋዛ ያልፈነዱ ቦምቦችን በማንሳት የፍልስጤም ግዛትን ታለማለች፤ታስውባለች ሲሉ ሃላፊነቱን መውሰድ እንደምትችልም ተናግረዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ሀገራት ቀደም ሲል ይህን ሃሳብ ውድቅ አድርገውት የነበረ ቢሆንም ትራምፕ ጋዛ እንደገና በምትገነባበት ወቅት ፍልስጤማውያን ከጋዛ ውጭ እንዲሰፍሩ ሃሳብ አቅርበዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደስልጣን ሲመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኟቸው የውጭ ሀገር መሪ ኔታንያሁ የትራምፕ ዕቅድ “ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ” ሃሳብ ነው ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም አምባሳደር ፍልስጤማውያን ወደ ጋዛ መመለስ እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ፥ ሃማስ በአንጻሩ የትራምፕን እቅድ “ተቀባይነት የሌለው” ሲል አጣጥሎታል።