Fana: At a Speed of Life!

ከአዲስ አበባ የሚነሱ 4 አዳዲስ የፍጥነት መንገዶችን ለመገንባት ጥናት እየተደረገ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚወጡ አራት አዳዲስ የፍጥነት መንገዶችን ለመገንባት ጥናት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በአስተዳደሩ የምህንድስና ግዥ ዳይሬክተር ፍሬው በቀለ (ኢ/ር) እንዳሉት÷ የፍጥነት መንገዶችን ከአዲስ አበባ ደሴ፣ ከአዲስ አበባ ጅማ ፣ከአዲስ አበባ ደብረማርቆስ እና ከአዲስ አበባ ነቀምቴ ነው ለመገንባት የታቀደው።

መንገዶቹ ከአዲስ አበባ የሚነሱና ተራራማ ቦታን የሚያልፉ እንዲሁም ደረጃቸው ከፍ ያሉ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ትልልቅ የቆረጣ ሥራ ያላቸውና ደረጃቸውና የመንገዶቹ ስፋት ከፍ ያለ በመሆኑ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃሉ ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቶቹን በመንግስትና የግል አጋርነት ትብብር ለመግንባት መታቀዱን ነው የገለጹት፡፡

የፕሮጀክቶቹ የአዋጭነት እንዲሁም መሰረታዊ የዲዛይንና የዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ሲሆን÷ለዝግጅት የሚያስፈልጉ የጥናት ሥራዎችም እየተጠናቀቁ መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ እያንዳንዳቸው በአማካይ ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው በመሆኑ በአንድ ጊዜ ሳይሆን በምዕራፍ ተከፋፍለው በተወሰነ ኪሎ ሜትር ብቻ ግንባታቸው እንደሚጀመር አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ጅማ እና አዲስ አበባ ደብረ ማርቆስ ፕሮጀክቶች ለገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት የግል አጋርነት ቦርድ እንደቀረቡ እና ቀሪዎቹም እንደሚቀርቡ አመልክተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት ግል አጋርነት ትብብር ከጸደቁ በኋላ ወደ ቀጣይ ሥራ ይሄዳሉ ነው የተባለው፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.