በስዊድን በደረሰ የሽብር ጥቃት የ11 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በስዊዲን ኦሬብሮ ከተማ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የሽብር ጥቃት የ11 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው አንድ መሳሪያ የታጠቀ ግለሰብ በኦሬብሮ የአዋቂዎች ትምህርት ቤት በመግባት በከፈተው ተኩስ መሆኑን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የኦሬብሮ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሮቤርቶ ኢድ ፎረስት÷ የጥቃት አድራሹ ዋነኛ አላማ እስካሁን በግልጽ አለመታወቁን ጠቁመው፣ወንጀለኛው በፀጥታ አካላት በተወሰደብት ርምጃ ሕይወቱ ማለፉን አረጋግጠዋል፡፡
በጥቃቱ ከሟቾች በተጨማሪ የተጎዱ ሰዎች ስለመኖራቸው አለመታወቁን የጠቆሙት የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ÷ የሽብር ጥቃቱን በተመለከተ ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚደርጉ ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው ከዋና ከተማዋ ስቶኮልም በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኦሬብሮ ከተማ መደበኛ ትምህርትን ማጠናቀቅ ያልቻሉ አዋቂ ሰዎች ትምህርት በሚከታተሉበት ት/ቤት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የስዊዲን ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ኪሪስቴርሶን በጥቃቱ እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው÷ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል ሲል ሬውተርስ ዘግቧል፡፡