በድልድይ መሰበር የተስተጓጎለውን የወልድያ- ቆቦ ትራንስፖርት ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከወልድያ ወደ ቆቦ የሚወስደው የብረት ድልድይ መሰበረን ተከትሎ የተስተጓጎለውን የትራንሶፖርት አገልግሎት ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የድልድዮችና ስትራክቸር ክፍል ዳይሬክተር ተክለስላሴ ንዳ (ኢ/ር) እንደገለፁት÷በአካባቢው የአሚድ ወንዝ የብረት ድልድይ ትናንት ከሰዓት በመደርመሱ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ መስተጓጎል ተፈጥሯል።
ከድልድዩ የመሸከም አቅም በላይ የጫነ አንድ ተሽከርካሪ ሲሻገር የብረት ድልድዩ መሰበሩን ጠቅሰው÷ የተፈጠረውን የትራንስፖርት መስተጓጎል ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ለማበጀት ወደ ስፍራው ማሽኖች ተልከውና ተለዋጭ መንገድ በፍጥነት ተሰርቶ ጊዜያዊ መፍትሄ መሰጠቱን ገልጸው÷በዚህም አሁን ላይ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች እንዲሸጋገሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የብረት ድልድዩን በሌላ ለመተካትና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠትም ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ እየተደረገ ነው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የብረት ድልድዩ 48 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን÷ከወልድያ ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት አሚድ ተብሎ በሚጠራ ወንዝ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡