Fana: At a Speed of Life!

የአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያ እና የመዝናኛ ስፍራ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያ እና የመዝናኛ ስፍራ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ተመርቆ በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ፥ ከተማዋን ውብ፣ ጹዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ዛሬ ለምረቃ የበቃው የአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያና መዝናኛ ስፍራ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አካባቢው ከዚህ ቀደም ለተሽከርካሪ፣ ለእግረኞችና ለአካል ጉዳተኞች መተላለፊያነት አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው ፥ አሁን ችግሩን በሚቀርፍና ዘመናዊነቱን በጠበቀ መልኩ መገንባቱን ገልፀዋል።

አካል ጉዳተኞችም በቀላሉ መተላለፍ የሚችሉበት የአሳንስር መጓጓዣ መኖሩንም ነው የተናገሩት።

በውስጡ የሀገር ውስጥ አልባሳት፣ መዋቢያዎች፣ ወርቅና ብር መሸጫ ቤቶች፣ የስልክ መሸጫዎች፣ የፈጣን ምግብ አገልግሎት እና መሰል የንግድ አገልግሎቶች መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርና የገቢ ምንጭ መሆን መጀመሩን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ነጻነት ዳባ በበኩላቸው፥ የመተላለፊያና የመዝናኛ ስፍራው በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ ብቁ አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ መገንባቱን ተናግረዋል።

ስፍራው እግረኞች በቀላሉ የሚያልፉበት ብቻ ሳይሆን አረፍ ብለው የሚዝናኑበትና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት ከመሆኑ አኳያ የአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያና መዝናኛ ስፍራን ተረክቦ በማስተዳደር ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ያደርጋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.